“በድላችን ላይ አንተኛ”

ከአራት ሳምንታት በፊት ወደ ግብጽ ስላቀናው እና በአይነቱ የመጀመሪያው ስለሆነው የኢትዮጵያ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ሁሉም በየፊናው የገባውን እና የተረዳውን ጀባ ብሎናል። አብዛኛው የልዑካን ቡድን አባላት በየስራ ዘርፉ ትዝብቱን ገልጿል። የቡድኑን አላማ እና ቆይታ እንዲሁም ጉብኝቱ የነበረውን ጠቅላላ ድባብ ለማወቅ የሪፖርተሩን አማረ አረጋዊ ጽሁፍን አሊያም በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮረፖሬሽን በዲፕሎማሲያችን ፕሮግራም የተላለፈውን ዝግጅት መመልከት እና ሌሎች በህትመት እና በኤሌክትሮኒክ ሚዲያ የወጡ ጽሁፎች እና የተላለፉ ፕሮግራሞችን ወደኋላ መልስ ብሎ መመልከቱ ስለቡድኑ ጠቅለል ያለ ግንዛቤ ለመያዝ በቂ ይመስለኛል።

እኔም እንደ አንድ የቡድኑ አባልነቴም ሆነ ጉዳዩን በቅርብ እንደሚከታተል ኢትዮጵያዊ የተሰማኝን ባካፍል ብዬ ከረፈደም ቢሆን ነቅቻለሁ። ስተኛ የነበረው ድል ላይ እንደነበረ ባወኩ ጊዜ ምናልባት አሁንም እንቅልፋቸውን ያልጨረሱትን ልቀስቅስ ብዬ እንዲህም አልኩ፣

የዚህ ቡድን ድል የሚለካው ካነገበው ግብ ጋር ሲነጻጸር ነው የሚል እምነት አለኝ። የቡድኑን አላማም ከላይ የተጠቀሱት ጽሁፎች እና ፕሮግራሞች በሚገባ የዳሰሱት ቢሆንም እኔም በተራዬ አላማው የነበሩትን እና ያልነበሩትን ነጥቦች በመጠቃቀስ ልጀምር።

በይዘቱ ከሞላ ጎደል ከሃገራችን የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ጋር ተመሳሳይ የሆነው የግብጽ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን እ.ኤ.አ በ2011 ዓ.ም በሀገራችን ጉብኝት ማድረጉ የሚታወስ ነው። በዚህም ወቅት የኢትዮጵያ መንግስት በናይል ወንዝ ዙሪያ ፍታሃዊ ተጠቃሚነትን የሚያሰፍነውን እና የግብጽ ወገን ያልፈረመውን የ CFA ስምምነት ግብጽ የአረቡን አብዮት ተከትሎ በወቅቱ ከነበረችበት የፖለቲካ ትኩሳት ተላቃ ቋሚ መንግስት እስክተመሰርት ድረስ እንዳይጸድቅ እና በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ ጥናት የሚያደርግ የአለም አቀፍ የኤክስፐርቶች ቡድን እንዲቋቋም ያለ ማንም ጥያቄ በወቅቱ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ እና በመንግስታቸው ተነሳሽነት ቃል ገብተው ነበር። በእርግጥ እነዚህ እርምጃዎች በኢትዮጲያ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ የማያሳድሩ እና ሃገራችን ከግብጽ ጋር ያላትን ልዩነት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ቁርጠኛ እንደሆነች ያሳዩ ነበሩ። የኛ ቡድንም በተራው ለሰፊው የግብጽ ህዝብ ሃገራችን በአባይ ወንዝ ላይ እየገነባችው ያለችው ግድብ የግብጽን ህዝብ እንደማይጎዳ የማስረዳት ተልዕኮ በማንገብ ነበር ወደ ግብጽ ያቀናው። በርግጥ ግድቡ በግብጽ ህዝብ ላይ ይህ ነው የሚባል ጉዳት የማያደርስ መሆኑ የፐብሊክ ዲፕሎማሲው ቡድን ምኞት ሳይሆን በአለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ በሆኑ የሳይንቲስቶች ቡድን ተረጋግጦ የቀረበ እውነታ ነው። የቡድኑ አላማም ይህንኑ እውነታ ለሚሰማው ሁሉ መናገር ነበር።

ይህ ቡድን ወደ ግብጽ ሲያቀና ከ80 ሚሊየን በላይ ግብጻዊ በአባይ ወንዝ ዙሪያ ያለውን የእውቀት ክፍትት በአምስት ቀን ቆይታው ሙሉ ለሙሉ ሊቀይር እንዳልሄደ ልብ ሊባል ይገባል። ለነገሩ አንድ የህዝብ የልዑካን ቡድን ለአምስት ቀናቶች በግብጽ ስለቆየ እና የተለያዩ የመንግስት ባለስልጣናትን እና የግብጽ ኅዝብ ተወካዮችን ስላገኘ ብቻ የግብጽ ህዝብ እና መንግስት ለዘመናት በአባይ ወንዝ ዙሪያ ሲገነባው የቆየውን የተሳሳተ አስተሳሰብ ይቀየራል አሊያም ሊቀይር ይገባል በሎ የሚያስብ አለ የሚል እምነት የለኝም- የቡድኑ አላማም አይመስለኝም!! በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ቡድን ከግብጽ ወገን ለሚነሱ ጥያቄዎች እና አጉል ጥርጣሬዎች ሁሉ መልስ ካልሰጠሁ በማለት አላስፈላጊ እንካ ሰላምቲያ ውስጥ ሊገባ እንዳልሄደም አምናለሁ።

እንግዲህ የዚህን ቡድን አላማ ማወቁ ድሎቹንም ሆነ ግድፈቶቹን ለመለየት ይረዳል እና እኔም ከአላማው አንጻር አርፍጄ የተገነዘብኳቸውን እና ስተኛባቸው የቆዩትን ድሎች ላካፍላችሁ።

ኢትዮጵያ አሁንም ልክ እንደድሮው በአባይ ወንዝ ዙሪያ የፍትሃዊ አጠቃቀም መርህን እንደምትከተል፤ የህዝቧን የመኖር ህልውና እየተፈታተነ የሚገኝውን ዋነኛ ጠላቷ ድህነትን ለመዋጋት የተፈጥሮ ሃብቷን የሌላ ሃገር ህዝብን ህልውና አደጋ ውስጥ በማይከት መልኩ መጠቀም እንደሆነ እንዲሁም ኢትዮጵያ ልየነቶችን በሰለጠነ መልኩ በመነጋገር መፍታት ፍላጎቷ እንደሆነ ይህ ልኡካን ቡድን በግብጽ ላገኛቸው ህዝብ ተወካዮች በፍጹም ኢትየጵያዊ አንድነት እና ጨዋነት አስረድቷል። ድል ቁጥር አንድ!

የአባይን ወንዝ አጠቃቀምን በተመለከተ በግብጽ ባለስልጣናትም ሆነ በሰፊው የግብጽ ህዝብ ዘንድ ያለውን አመለካከት በአካል ተገኝቶ መገንዘብ መቻሉ እና ይህም በቀጣይ በአባይ ወንዝ አጠቃቀም ዙሪያ መንግስታችን ከሚደርስባቸው ውሳኔዎች ጎን በመቆም በግብጻዊያን ዘንድ ያለውን የተዛባ አመለካከት ባገኘው አጋጣሚ እና በየሞያ ዘርፉ መወጣት ያለበትን ሁሉ እንዲወጣ መገንዘቡ። ድል ቁጥር ሁለት!

ለኢትዮጵያና ለግብጽ ህዝብ እና ፖለቲከኞች ከሚያስተላልፈው መልዕክት ባልተናነሰ መልኩ የናይል ወንዝን አጠቃቀም በቅርበት ለሚከታተለው ለአለምአቀፉ ማህበረሰብ ኢትዮጵያ አሁንም ቢሆን ለመልማት እና ህዝቦቿን ከድህነት ለማላቀቅ በምታደርገው ጥረት የትኛውንም ሃገር የመጉዳት ፍላጎት እንደሌላት እና በወንዙ አጠቃቀም ዙሪያ ያሉት አለመግባባቶችም በሰላማዊ መንገድ ይፈቱ ዘንድ ምኞቷ እንደሆነ፣ ይህ የመልማት ጉጉት ደግሞ በኢትዮጵያ መንግስት ወይም በገዢው ፓርቲ ዙሪያ ብቻ የታጠረ ሳይሆን የሁሉም ኢትየጵያዊ ህልም እንደሆነ በማስመልከት ቡድኑ ያስተላለፈው ጉልህ መልዕክት ሊረሳ የሚገባው ጉዳይ አይደለም። ድል ቁጥር ሶስት!

በርግጥ ይህ ስብጥር የተለያየ የሃገራችን የማህበረሰብ ክፍልን እና የተለያየ አመለካከት ያላቸውን ሁሉ እንደመወከሉ ይዘቱ በራሱ ለሃገራችን ህዝብ የሚያስተላልፈው መልዕክት እንዳለ ይሰማኛል። ይህም በልዑካን ቡድኑ አባላት እና በሞያ አጋሮቻቸው ዘንድ የሚፈጥረው ”ለካ እኔም በሃገሬ ወሳኝ ጉዳይ ፋይዳ ያለኝ ሰው ነኝ” መንግስት የሚያደርገውን አገራዊ የልማት እንቅስቃሴ ለመደገፍ በዲፕሎማሲው መስክም የበኩሌን መወጣት እችላለሁ የሚል አስተሳሰብ ማስረጹ እና በወሳኝ ሃገራዊ ጥቅሞቻችን ዙሪያ ልዩነት እንደሌለን አመላካች ነበር። ድል ቁጥር አራት!

ከዚህ ጋር በተያያዘ ይህ ቡድን መንግስት የሃገራችንን ብሄራዊ ጥቅም ከማስጠበቅ አንጻር በተለመዶው መንገድ የሚያራምደውን የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ በዘላቂነት በማገዝ የሃገሪቷን የዲፕሎማሲ አድማስ እንደሚያሰፋ አምናለሁ። ከዚህ ጋር በተያያዘ የሃገራችን ጠቅላይ ሚኒስትር የቡድኑን ቆይታ በገመገሙበት ወቅትም ከልዑኩ አባላት የመጣውን የ ‘ይህ ቡድን በዘላቂነት የሃገራችንን ብሄራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ይችል ዘንድ ተቋማዊ ይሁን’ ጥያቄ በደስታ የተቀበሉት በመሆኑ የሃገራችን ዲፕሎማሲ በህዝብ የተደገፈ እንዲሆን በር ከፍቷል። ይህንንም ለማሳካት የልኡካን ቡድኑ አባላት ቀረቤታቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል። ድል ቁጥር አምስት!

እንግዲህ ይህ ቡድን በመጀመሪያ ተልእኮው ያስገኘው ድል ከዚህም በላይ ሊሆን እንደሚችል አምናለው። እነዚህን በመጀመሪያው ምዕራፍ የተገኘ ስኬቶች ቀጣይነት ያላቸው እንደሆኑ ለማድረግ እና የሃገራችንን ልማት በተፋጠነ መልኩ ለማስቀጠል መንግስትም ሆነ ሰፊው ህዝብ ከፍተኛ ሃላፊነት እንዳለበን ይሰማኛል። ከዚህም በላይ የዚህ የፐብሊክ ዲፕልማሲ ቡድን አስፈላጊነት ከሃገራችን እድገት ጋር አብሮ የሚያድግ እንደመሆኑ ይህ ቡድን ከዚህም በላይ በመጠናከር ለሃገራችን ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ ሁነኛ ደጋፊ ሊሆን ይገባል ባይ ነኝ።

በመጨረሻም የዚህ ቡድን የመጀመሪያ የቤት ስራ እንከን የለሽ ነው በማለት ከመዘናጋት ይልቅ ቡድኑ ያስመዘገባቸውን ድሎች አጠናክሮ በማስቀጠል እና የታየ ክፍተቶችን በመድፈን አገራዊ ፋይዳውን ማጠናከር ያስፈልጋል እያልኩ ይህ ቡድን ከግብጽ ከተመለሰ በኋላ በተገናኘበት መድረክ ከቀረበ ንግግር በጣም ከማረከኝ እና ለጽሁፌም ርዕስ በሆነኝ አርቲስት ደበሽ ተመስገን ክቡር ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህንን በመጥቀስ በተናገረው ጽሁፌን ልቋጭ። “ይህ የድል ዘመናችን ነው፤ በድላችን ላይ አንተኛ”

 

 

 

3 thoughts on ““በድላችን ላይ አንተኛ”

  1. Good observations Fitse. I like the way you put the ‘Goals of the Mission’ first and then the ‘Achievements’. One thing that bothered me though is the request of the ‘Team’ to make it ‘institutional’. ‘…ይህ ቡድን በዘላቂነት የሃገራችንን ብሄራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ይችል ዘንድ ተቋማዊ ይሁን…’. I am not clear with the request. I believe such public diplomacy actions should be consistent but I also believe the composition of the team may and should change from time to time as we may need to bring in some more new and qualified faces in to the team. Cheers.

    Like

    1. Thank you so much for your considerations Sam. ጥያቄህን በተመለከተ ይህ ቡድን በዘላቂነት ተቋማዊ ይሁን ሲባል አባሎቹ እንዳሉ ይቀጥሉ ለማለት ሳይሆን በሃገራችን ደረጃ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድኑ እንደ ቡድን በቋሚነት፣ እንደ ይዘት ደግሞ ተሻሽሎ በመቅረብ የሃገራችንን ብሄራዊ ጥቅም ማስጠበቅ አለበት ከሚል ነው። ስለዚህ አንተም እንዳልከው ይህ ቡድን ከዚህ የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።

      Like

Leave a comment