“እስኪ መንግስትን እንቃወም”

ተጻፈ በ Fere Zer
 ዛሬ ደግሞ ከጓደኛዬ ከገዳሙ ጋር ስንጨዋወት “ፊደል የቆጠረና ከተማ-ቀመስ የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ሁለት ዋና ዋና “ሆቢ”ዎች እንዳሉት አረጋግጫለሁ፣ እነሱም እግር ኳስና መንግስትን መቃወም ናቸው።” አለኝ። እኔም ግራ ገባኝና “ስትል? ደርግን ማለትህ ነው?” ስል ጠየኩት። “ኖ ኖ! የትኛውንም ቤት ያፈራውን መንግስት ማለቴ ነው።” አለና ሊያብራራልኝ ገባ። “አየህ ጥንት የመንግስትን ስም በክፉ ማንሳት ፈጽሞ ነውር ነበር። በተለይ ከ1960ዎቹ የተማሪዎች ንቅናቄ ጀምሮ ደግሞ መንግስትን በመልካም ማንሳት ፈጽሞ ነውር የሆነ ይመስላል። ቀልደኛው መንግስትን ጎንተል ካላደረገ እንጀራው የተጋገረ አይመስለውም። ደራሲው እዚህ ግባ ማይባል ነገር ይጽፍና መጨረሻ ላይ ትንሽ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጎሸም የምታደርግ ነገር ሲጨምርባት ገበያ ደራ በለኝ። አንዳንዶቹ ጭራሹኑ መንግስትን መሳደብ የህይወት ዘመን ጥሪ አድርገው የተቀበሉት ይመስላል። ስለዚህ በተዘዋዋሪ መንገድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የስራ እድል እየፈጠሩ ነው ማለት ነው። ዋናው ስራ መፈጠሩ ነው…” እያለ ሲቀጥል አቋረጥኩትና “መንግስትን ዝንቡን እርሽ አትበሉት ነው ምትለኝ?” አልኩት። “አይደለም። መንግስትን መተቸት የወግ ነው። ነገር ግን ዝም ብሎ በግድቡም በድርቁም እኩል መተቸት ጤነኛ አይደለም ነው ምለው። ለምሳሌ አንድ ወዳጄ ባቡር ሊሰራ ነው ሲባል ሲሰማ “ወጉም አልቀረ” ብሎ አፌዘ። በኃላ ተጀምሮ እየተሰራም “ውሸት ነው! የማይጨርሱትን ጀምረው” እያለ አወራ። አሁን የምር ሆኖ ባቡሩ አልቆ ስራ ሲጀምር ማመን ስላልፈለገ ባቡሩ በማያልፍባቸው መስመሮች ነው እየመረጠ ሚንቀሳቀሰው። ይኼን የመሳሰሉትን ነው አየህ…እእእ… ክሪስትያኖ ሮናልዶ ስፔን ላይ ሪጎሪ ሲስት እዚህ የኛ መንግስት ጉዱ ይፈላል። ለምን? በቃ መንግስት ነዋ። መንግስት በጥራት ቢያስተላልፈውና ቴሌቪዥኑ ብዥ ባይል ኖሮ አይስተውም ነበር። በጉባ ላፍቶ ወረዳ ዝናብ ለተወሰኑ ሳምንታት ከተቋረጠ ጠቅላይ ሚኒስትሩን አያርገኝ!። ከመላዕክት ጋር በቂ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ስላላደረጉ ነዋ ዝናቡ የቆመው። እ…” ብሎ ሌላ ምሳሌ ሊያመጣ ሲንደረደር ጣልቃ ገባሁና

“ምክንያቱ ግን ምን ይመስልሃል?” አልኩት። “ወደሱ ልመጣልህኮ ነው” አለና ቀጠለ።
“እንግዲህ እንደኔ ሶስት ዋና ዋና ምክንያቶችን ማስቀመጥ ይቻላል። አንደኛ የኢትዮጵያ ህዝብ ከባርኔጣ በስተቀር ምንም ነገር ራሱ ላይ ሲወጣ አይወድም። ሁልጊዜ የበላይ መሆን ነው ‘ሚፈልገው። ለምሳሌ ሰው ቤት እንግድነት ስንጠራ ከመደቡ ወይም ከወንበሮቹ በላይኛው ክፍል መቀመጥና በታች መቀመጥ ለአንድ ኢትዮጵያዊ ከፍተኛ ልዩነት አላቸው። በሌላ በኩል አንድ ኢትዮጵያዊ ኢንቨስተርን ከላይኛው አዋሽ ነው ወይስ ከታችኛው አዋሽ መሬት ምትፈልገው ብትለው ሁለቱንም ባያውቃቸውም በእርግጠኝነት የላይኛው አዋሽን ይመርጣል። በላይ ዘለቀ ነው እንጂ በታች ዘለቀ ብሎ ስም አታገኝም። በቃ! ኢትዮጵያዊ በላይኛው እንጂ በታችኛው መስመር እንዲዘልቅ አይፈለግም።
ሁለተኛ በረጅሙ ታሪካችን በብዙ ጦርነቶች ተጋድለን ነጻነታችንን አስጠብቀን የቆየን ስለሆንን ነው መሰለኝ በቃ መመራት የሚባል ጽንሰ-ሃሳብን ከውስጥም ሆነ ከውጭ አውልቀን መጣል እንፈልጋለን። እርግጥ ነው ይኼ ያለመገዛት ባህሪያችን አድዋን ወልዷል። ሌሎች ወራሪዎችን ሁሉ ድባቅ መቷል። በአምስቱ አመት የጣሊያን ወረራ ወቅት ጠላትን መቆሚያ መቀመጫ አሳጥቷል። ክፋቱ ግን ሁላችንም በአንዴ ነው መጓዝ ምንፈልገው። ጥቂቶች ከፊት ሆነው እንዲመሩን ስለማንፈቅድ መንገዱ እየጠበበ ከነዐን መድረስ አልቻልንም።
ሶስተኛ መንግስትን መቃወም የምሁርነትና የአስተዋይነት፣ ከተራው ሰው ጋርም ያለመደመር ምልክት ተደርጎ ይቆጠራል። በዩኒቨርስቲ ስታስተምር “ወደ እኛ አገር ስንመጣ ግን…” ብለህ መንግስትን እንዳይሞት እንዳይሽር አድርገህ ስትደበድበው በቃ አንተ በተማሪዎችህ ዘንድ የበቃህና የነቃህ ምሁር ነህ።” አለኝ።

ምንም ጥናት ሳያደርጉ “ፊደል የቆጠረው የኢትዮጵያ ህዝብ” ብሎ እንደዚህ መፈረጅም ሆነ “ሶስት ዋና ዋና ምክንያቶች” እያሉ መደምደም የሚቻል መሆኑን እርግጠኛ ስላልሆንኩ ልክ ነህም ተሳስተሃልም አላልኩትም።

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s