የህዳሴው ትውልድ በተስፋዬ መሰለ

የህዳሴው ትውልድ

ታሪክን ቀይረህ ታሪክ የሰራሀው
ጨለማን በመግፈፍ ጮራን ያበራሀው
ፍርሃቴን መንጥረህ ተስፋን የዘራሀው
ዛሬ በዓለም ፊት እኔን ያኮራሀው
የህዳሴው ፋና አንተ ጀግናው ትውልድ
በእውነት ካንጀቴ አደረኩህ ውድድ!

ሌት ተቀን በመስራት እንዲህ እየታተረ
ታዕምር ለመፍጠር ሩቅ እያማተረ
ይሄ ቆራጥ ትውልድ ጀግናን የፈጠረ
ጉዞውን ሊጀምር ድል እያስቆጠረ
በእውነት ሜዳ ውለው በእውነት ያላደሩ
ያኔ ቢሳለቁም አይችሉም እያሉ
እያዩት ነው ዛሬ ሲተገበር ቃሉ!
በስንት ዘመናት አንዴ የሚወለድ
ለካስ ትውልድ አለ እንዲህ የሚወደድ!

በቁጭት ተነስቶ ግሎ እንደነበልባል
አባይን በመድፈር ግድብ ይገነባል
ለካስ ጀግና ትውልድ የሩቁን ያቀርባል
እናም በመሆኔ የዚህ ትውልድ አባል
ታዲያ ምን ይገርማል እድለኛ ብባል!

ሆኖ እንዳልነበረ የበረሃው ሲሳይ
እኔን ሲያማርረኝ የጨለማው ሲቃይ
ወገኔን ሲያረግፈው ያ ረሃቡ ገዳይ
ዛሬ ይደንቀኛል አባይን እንዲህ ሳይ!
የአባይ ፍሬ ዱካ ያኔ እንደተዘራ
ዝንታለም ተዘፍኖ ዝንታለም ተወራ
አዎ! ያባይ ፍሬ ካፈር ተደባልቆ
አልበቅል እያለ ስንት ትውልድ አልቆ
በሀሳብ ባክኜ ስጓዝ እየዋኘሁ
ናፍቄ ጓጉቼ ብዬ የት ባገኘሁ
ድንገት ጀግና ትውልድ ድንጋይ ፈነቀለ!
እናም በጉባ ላይ ትልቅ ዝናም ጣለ
ያ የጠፋው ፍሬ ስመኘው በቀለ!

የህዳሴው ግድብ ሲጣል መሰረቱ
መለስ ብለን ስናይ ልዩ ነው ስሜቱ!
በክንዱ ሰባብሮ ጠንካራውን አለት
ዛሬ የጣለልኝ የነገን መሰረት
ድህነትን አርጎ ታሪክ ተረት ተረት
ዘላለም ወደድኩት አይደለም የወረት
ጠዋት ያሰበልኝ ገና የማታውን
በምን ልመልሰው ታዲያ ውለታውን
ሰው ያደረገኝን ይህን አኩሪ ትውልድ
በቃ ዝም ብዬ ባደርገውስ ውድድ!
በቃ ዝም ብዬ አደረኩት ውድድ!

ለህዳሴው ግድብ ሳይቆጥብ የኪሱን
በእውቀት በገንዘብ በጉልበት ገሚሱን
ሳይለምን ሳይከጅል ሳይናፍቀው የሰው
ራሱ ማህንዲስ ሆኖ ራሱ በቀየሰው
አባይን አዙሮ እንዲያይ ላስገደደው
ማን አለ ይህን ትውልድ ታዲያ ያልወደደው
ከልክ ያለፈ ነው ለሱማ መውደዴ
ጠብ እርግፍ! እንስፍስፍ! ይልለታል ሆዴ
አወድሰዋለሁ ራሴን አሳንሼ
እድሜ ላበድረው ከራሴ ቀንሼ

በተባበረ ክንድ በአንድ ሜዳ ውሎ
እራሱን በመስጠት ራሱን አገልግሎ
እንደ አገር ተወካይ እንደ ዲፕሎማት
ትውልዴን ወክዬ ቃሌን ለማሰማት
ላደረገኝ ትውልድ እንዲቃና አንገቴ
ምን ያንሰዋል እስኪ ብወደው ካንጀቴ!
ታዲያ ምን ያንሰዋል ብወደው ካንጀቴ!

እኔም እወጣለሁ የውጭውን ጉዳይ
እድገቷ እንዲፋጠን ልክ እንደ እንጉዳይ
በደንብ እሞላለሁ የ አገሬን ሙዳይ

ይህን እንቁ ትውልድ ጋሻዬ አድርጌ
የልማትን ሚስጥር አገኘሁ ፈልጌ
ማጣጣም ችያለሁ በቅሎልኛል ግጌ
ተስፋ ሞልቶበታል ሁሉም ጥጋጥጌ
ግግ ቢኖረኝም አልነክስም ለምዝጌ
አብረናችን የሚል ፍትሐዊ ነው ህጌ
ሲጠቀም የራስጌው አይጎዳም ግርጌ!

የህዳሴን ዘመን ያኔ ስናበስር
እኛ ብቻ አትርፈን ሌላው እንዲከስር
አይደለም በፍጹም ስንፈትሸው ከስር
ለማምጣት ነው እንጂ ጠንካራ ትስስር
ተያይዞ ማደግ አብሮ ለመሻገር
አንዳችን ላንዳችን ሆነን ጥሩ ማገር

የብዙ ዘመናት የ አባይ ላይ ህልሜን
እንዲፈታ አድርጎ ላሳወቀኝ ስሜን
ለዚህ እንቁ ትውልድ ልዩ ነው ክብሬ!
ህዳሴ ግድብን ስጎበኘው ዛሬ

ለፍራትም ያለመፍራት መድሃኒቱን
ያስቀመጠው በትንበያ ወደፊቱን
ለአባይም ያበጀለት ማረፊያውን
አስፈሪውን የከፈተ ማለፊያውን
እስከመቼ በጨለማ በመዳበስ
እስከመቼ በጭስ ነፋስ መጨናበስ!
ብሎ ልብ ገዝቶ ወኔ አፍርቶ
የአንድነት ሀይል-ክንዱን አበርትቶ
ያ ጽልመቱ ተገፎልኝ ድህነቴ እንዲወገድ
ላደረገኝ ዳግም በህይወት እንድወለድ
ይገበዋል ለዚህ ትውልድ ፍቅር-መውደድ!

ቀስቃሽ ሆኖ ከእንቅልፌ ያነቃኝን
ቤዛ ሆኖ ለዚህች ቀን ያበቃኝን
በራስ አቅም በራስ ጥረት
ያፈለቀውን የ ብርሃን ፍሰት ጅረት
በጀግንነት በብርታቱ ተገርሜ
በቃ! ወደድኩታ ይህን ትውልድ ደጋግሜ!

ከዚህ ወዲያማ ላዓለም ሰላም እየዘመርን
ልማት እድገት እየደመርን እየጨመርን
በመጨረስ ታላቅ ግድብ እንደጀመርን
ታላቅ አገር እንፈጥራለን፤ ያኔም ታላቅ እንደነበርን!
ታላቅ አገር እንፈጥራለን፤ ያኔም ታላቅ እንደነበርን!

ተስፋዬ መሠለ
ግንቦት 2006 ዓ/ም

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s