አቶ ሀይለማርያምና የማህበራዊ ድህረ ገጽ ተቺዎቻቸዉ

By Awet Gebrekiristos

ጠቅላይ ሚኒስተር ሀይለማርያም ለኬንያዉ አቻቸዉ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ባዘጋጁት የእራት ግብዣ (State Dinner) ያሳዩትን ዉዝዋዜ አስመልክቶ የተለያዩ አስተያየቶች በተለያዩ ማህበራዊ ድህረገጾች ስመለከት ነበር፡፡

የተሰጡት አስተያየቶች በዚህ መልኩ ሊጠቃለል ይችላል፡- “መሪ እንደዚህ መሆን የለበትም፣ እንዲህ በማድረጉ ለኬንያና ኢትዮጵያ ግንኙነት የሚጨምረዉ ነገር አይኖርም፣ ሀይማኖቱ አይፈቅድለትም ወዘተ” የሚሉ ናቸዉ፡፡ አስተያየቶቹ የተሰጡበት ምክንያትና መነሻ አድበስብሶ ከማለፍ ይልቅ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ድርጊት ከፖለቲካ ባህለችንና ከሚኖረዉ አንድምታ አንጻር ተንትኖ ማየት ግድ ይላል፡፡ …

የፖለቲካ ባህላችን

ስለ ፖለቲካ ባህላችን (Political Culture) ብዙ ነገር ማለት ይቻላል፡፡ ለአሁኑ ግን ከኛ የፖለቲካ ባህል ዕይታ “መሪ እንዴት ነዉ መሆን ያለበት?” የሚለዉን እንመልከት፡፡ አገራችን ለብዙ ዘመን በፊዉዳል አስተዳደር የቆየች እንደመሆንዋና፣ በወታደራዊ መንግስት ለ17 ዓመታት የተገዛን እንደመሆናችን መሪን በህዝቡ ፊት ቆፍጠን፣ ኮስተር፣ ኩፍስ ብሎ እንዲታይ እንጠብቃለን፡፡ ከዚህም አልፎ እብሪተኝነትንና ትእቢትን እንደ አንድ የመሪነት መለኪያ (Quality of Leadership) አድርገን የሚንወስድ ኢትዮጵያዊያን ጥቂቶች አይደለንም፡፡

ዐይኖቹን እያጉረጠረጠ “ቂጣቸዉን ወግተን አባረርናቸዉ” የሚል መሪ የለመድን ሰዎች ትህትና በተሞላበት አንደበት መግለጫ የሚሰጥ ጠቅላይ ሚኒስተር ግርማ ሞገስ (Charisma) የጎደለዉ ሆኖ ይታየናል፡፡ ተኮፍሰዉ ተቀምጠዉ አንጀባቸዉ ለሥራም ለእንግዳም የማይጥም ንጉስ የለመደ አዕምሮ ቆሞ በአገሩ ባህል የአገሩን ዲፒሎማሲ ሥራ የሚሰራ መሪ መቀበል ያዳግተዋል፡፡ በአጭሩ ተገልጋይ መሪ እንጂ አገልጋይ መሪ መቀበል ይሳነናል፡፡

አገራዊ ክብር

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጎረቤት አገር ህዝብ መሪ በአገሩ ባህልና ጭፈራ መታየቱ “አዋረደን፣ አፈርን” የሚሉ እንድምታ ያላቸዉ አስተያየቶች በብዛት ተንጸባርቀዋል፡፡ መጠየቅ ያለብን ‘ለምን እና ማን ፊት ነዉ የተዋረድነዉ?’ የሚለዉን ነዉ፡፡ ሰማይ ላይ የተንሳፈፈ የክብር ትርጉም ለራሳችን እየሰጠን በትንሹም በትልቁም “ተዋርደናል፣ ተደፍረናል” እያልን የምንደነፋ ሰዎች የቀን መቁጠሪያችን በ21ኛዉ ክፍለዘመን ማስተካከል ይጠበቅብናል፡፡

ሀይማኖትና መንግስት

አንዳንዶቻችን አቶ ሀይለማርያም የንሳሃ አባታችን ይመስለናል ልበል? ከመቼ ጀምሮ ነዉ የአንድ መንግስትና ሀየማኖት የተለያዩበት አገር (Secular State) መሪ በመጽሀፍ ቅዱስና ቅዱስ ቁርዓን መገምገም የጀመርነዉ? አረ በማንከተለዉ ሀይማኖት ገብተን ይበልጥ ተቆርቃሪ በመምሰል የፖለቲካ ትርፍ ለማጋበስ የምንላላጠዉንስ ምን እንባል ይሆን?

ዲፕሎማሲ (Personal Diplomacy)

በዲፕሎማሲዉ መስክ መሪዎች እንደ ግለሰብ በመካከላቸዉ የሚኖር መልካም ሆነ የሻከረ ግንኙነት ለሚወክሉት ህዝብና አገር ይተርፋል፡፡ የአሜሪካዉ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽ ከሩሲያዉ ፑቲን ጋር የፈጠሩት መቀራረብ ሁለቱም አገሮች በእሳቸዉ ሥልጣን ዘመን ላሳዩት አንጻራዊ መልካም ግንኙነት መሠረት እንደነበረ ይገልጻሉ፡፡ አቶ ሀይለማርያምም ከኡሁሩ ኬንያታ ያደረጉት ይህንኑን ነዉ፡፡ ከጎረቤቶቻችን ጋር በጋራና በተናጠል ለምንሠረዉ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ጸጥታዊ ትብብር መሰረት ነዉ የጣሉት፡፡

“የአራደነት ብልጫ” እና የማህበራዊ ድህረ ገጽ ተቺዎች

አቶ በረከት ስምኦን “የሁለቱ ምርጫዎች ወግ” በሚለዉ መጽሀፋቸዉ “የአራዳነት ብልጫ የሚሰማዉ” ብለዉ የገለጹት ዶ/ር ብርሃኑ ነጋን ነበር፡፡ የአራዳነት ብልጫ የሚሰማቸዉ ፖለቲከኞችና ተቺዎች በብዛት የሚታዩበት የኢትዮጵያ ፖለቲካ፣ ትችቶቻችን በመርህ ላይ ያልተመሰረቱና ለአገሪቱ መጪዉ ጊዜ ቅንጣት ታህል አስተዋጽኦ ማድረግ የማይችሉ ሆነዉ እናገኛቸዋለን፡፡
የአንድ መሪ ወይም መንግስት ድርጊት ከአጠቃላይ የአገሪትዋ ፖለቲካዊ ወይም ኢኮኖሚያዊ ጉዞ (The Bigger Picture) ተንትኖ የሚኖረዉ ተጽእኖ ከማስረዳት ይልቅ እንደ ተራ የሰፈር ጎረምሳ ትንኮሳቸዉን የሚሰነዝሩ ተችዎች በየድህረገጹ መበራከታቸዉ ለምክንያታዊ የፖለቲካ ዉይይቶች መዳበር ዕንቅፋት ሆነዉ ይገኛሉ፡፡

“የአራዳዎች” ትችት መበራከት አንድም ከዕዉቀት ማነስ የሚመነጭ ሲሆን ሌላዉ የፖለቲካ ሥልጣን በተፈጥረዉ በነሱ እጅ ብቻ የሚያምር ከሚመስላቸዉ የዋህ ዜጎች ነዉ፡፡ በሶስተኛ ደረጃ ሊመደቡ የሚችሉት ጥቂቶች ግን በማህበራዊ ድህረ ገጾች ተነባቢነት ወይም ተሰሚነት የሚገኘዉ አጉዋጉል ቀልዶችና ትችቶች በመፈብረክ መሆኑን የሚያምኑትና ብዙ ’Like’ ከማስደረግ ያለፈ ዓላማ የሌላቸዉ ናቸዉ፡፡ ሁሉም የሚያመሳስላቸዉ ነገር ቢኖር ግን በዚች አገር ፖለቲካ “አራዳዎች” መሆናቸዉንና ዕርባናቢስ መሆናቸዉ ነዉ፡፡

በመጨረሻም፡

በዚህ አጋጣሚ የፖለቲካ ሥልጣን በእጃችሁ እስኪወድቅ ሳትጠብቁ፣ ብዙ ’Like’ የማግኘት ዓላማ የሚሻገር የአገራችንን መጪ ጊዜ አስባችሁ፣ የአጉራዘለል የፌስቡክ አብዮተኞችን ስድ አፍ ተቀዋቁማችሁ፣ በዕዉቀትና በአመክንዮ አስደግፋችሁ ገንቢ አስተያየትም ሆነ ትችት ለምታቀርቡልንና ለምታስተምሩን ሁሉ ማመስገን ግድ ይለናል!!!

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s